ሰበር ዜና: ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስራ መልቀቂያ አስገቡ

Fana

ሰበር ዜና
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስራ መልቀቂያ አስገቡ

Image may contain: 1 person, sitting, suit and indoor

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሀላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለመነሳት መልቀቂያ አስገቡ።

አቶ ኃይለማርያም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ መልቀቂያቸውን ለኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስገባታቸውን እና ምክር ቤቱም ጥያቄያቸውን ይቀበላል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

ከደኢህዴን ሊቀመንበርነት ለመነሳት ለንቅናቄው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅርበው እንደተቀበላቸው እና ይህም ለማዕከላዊ ኮሚቴ ቀርቦ ይፀድቃል ብለው እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት።

ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄም በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ማግኘቱን የገለጹ ሲሆን፥ ለግንባሩ ምክር ቤት መልቀቂያ ማስገባታቸውንም አስታውቀዋል።

አቶ ኃይለማርያም በሀገሪቱ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ለመስጠት የቻሉትን ማድረጋቸውን ተናግረው፥ አሁን ስልጣን የሚለቁትም የችግሩ መፍትሄ መሆን ስለፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የስልጣን ሽግግር እስከሚደረግ ድረስም በስራቸው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልፀዋል።
የሀገሪቱ ህዝቦች በተለይም ደግሞ ወጣቶች ሀገሪቱ የምትታወቅበትን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንዲወጡ አደራ አስተላልፈዋል።

በካሳዬ ወልዴ እና ዳዊት መስፍን